Genesis 43
World English Bible (en) → Amharic Bible (am)
- 1
፤ራብም በምድር ጸና።
- 2
ከግብፅም ያመጡትን እህል በልተው ከፈጸሙ በኋላ አባታቸው። እንደ ገና ሂዱ፤ ጥቂት እህል ሸምቱልን አላቸው።
- 3
ይሁዳም እንዲህ አለው። ያ ሰው። ወንድማችሁ ከእናንተ ጋር ካልሆነ ፊቴን አታዩም ብሎ በብርቱ ቃል አስጠነቀቀን።
- 4
ወንድማችንን ከእኛ ጋር ብትሰድደው እንወርዳለን፥ እህልም እንሸምትልሃለን፤
- 5
ባትሰድደው ግን አንሄድም፤ ያ ሰው። ወንድማችሁ ከእናንተ ጋር ካልሆነ ፊቴን አታዩም ብሎናልና።
- 6
እስራኤልም አላቸው። ለምን በደላችሁኝ? ለዚያውስ። ሌላ ወንድም አለን ብላችሁ ለምን ነገራችሁት?
- 7
እነርሱም አሉ። ያ ሰው ስለ እኛና ስለ ወገናችን ፈጽሞ ጠየቀን እንዲህም አለን። አባታችሁ ገና በሕይወት ነው? ወንድምስ አላችሁን? እኛም እንደዚሁ እንደ ጥያቄው መለስንለት፤ በውኑ። ወንድማችሁን አምጡ እንዲለን እናውቅ ነበርነን?
- 8
ይሁዳም አባቱን እስራኤልን አለው። እኛና አንተ ልጆቻችንም ደግሞ እንድንድን እንዳንሞትም ብላቴናውን ከእኔ ጋር ስደደው፥ እኛም ተነሥተን እንሄዳለን።
- 9
እኔ ስለ እርሱ እዋሳለሁ ከእጄ ትሻዋለህ፤ ወደ አንተ ባላመጣው፥ በፊትህም ባላቆመው፥ በዘመናት ሁሉ አንተን የበደልሁ ልሁን።
- 10
ባንዘገይስ ኖሮ አሁን ሁለተኛ ጊዜ በተመለስን ነበር።
- 11
እስራኤልም አባታቸው እንዲህ አላቸው። ነገሩ እንዲህ ከሆነስ ይህንን አድርጉ፤ ከተመሰገነው ከምድሩ ፍሬ በዓይበታችሁ ይዛችሁ ሂዱ፥ ለዚያም ሰው እጅ መንሻ፥ ጥቂት በለሳን፥ ጥቂት ማር፥ ሽቱ፥ ከርቤ፥ ተምር፥ ለውዝ ውሰዱ።
- 12
ብሩን በአጠፌታ አድርጋችሁ በእጃችሁ ውሰዱ፤ በዓይበታችሁ አፍ የተመለሰውንም ብር መልሳችሁ ውሰዱ፤ ምናልባት በስሕተት ይሆናል።
- 13
ወንድማችሁንም ውሰዱ፥ ተነሥታችሁም ወደዚያ ሰው ተመለሱ።
- 14
ሁሉን የሚችል አምላክም ሌላውን ወንድማችሁንና ብንያምን ከእናንተ ጋር ይሰድድ ዘንድ በዚያ ሰው ፊት ምሕረትን ይስጣችሁ፤ እኔም ልጆቼን እንዳጣሁ አጣሁ።
- 15
ሰዎቹም በእጃቸው ያችን እጅ መንሻና አጠፌታውን ብር ብንያምንም ወሰዱ፤ ተነሥተውም ወደ ግብፅ ወረዱ፥ በዮሴፍም ፊት ቆሙ።
- 16
ዮሴፍም ብንያምን ከእነርሱ ጋር ባየው ጊዜ የቤቱን አዛዥ እንዲህ ብሎ አዘዘው። እነዚያን ሰዎች ወደ ቤት አስገባቸው፥ እርድም እረድ አዘጋጅም፥ እነዚያ ሰዎች በእኩለ ቀን ከእኔ ጋር ይበላሉና።
- 17
ያ ሰውም ዮሴፍ እንዳለው አደረገ፤ ያ ሰውም ሰዎቹን ወደ ዮሴፍ ቤት አስገባ።
- 18
እነርሱም ወደ ዮሴፍ ቤት ስለ ገቡ ፈሩ፤ እንዲህም አሉ። በዓይበታችን ቀድሞ ስለ ተመለሰው ብር ሊተነኰልብን ሊወድቅብንም፥ እኛንም በባርነት ሊገዛ አህዮቻችንንም ሊወስድ ወደዚህ አስገባን።
- 19
ወደ ዮሴፍ ቤት አዛዥም ቀረቡ፥ በቤቱም ደጅ ተናገሩት፥
- 20
እንዲህም አሉት። ጌታዬ ሆይ፥ ቀድሞ እህልን ልንሸምት ወርደን ነበር፤
- 21
ወደምናድርበትም ስፍራ በደረስን ጊዜ ዓይበታችንን ከፈትን፥ እነሆም፥ የእያንዳንዱ ሰው ብር በየዓይበቱ አፍ እንደ ሚዛኑ ብራችን ነበረ፤ አሁንም በእጃችን መለስነው።
- 22
እህል እንሸምትበት ዘንድ ሌላም ብር በእጃችን አመጣን፤ ብራችንንም በዓይበታችን ማን እንደ ጨመረው አናውቅም።
- 23
እርሱም አላቸው። ሰላም ለእናንተ ይሁን፥ አትፍሩ፤ አምላካችሁና የአባታችሁ አምላክ በዓይበታችሁ የተሰወረ ገንዘብ ሰጣችሁ፤ ብራችሁስ ደርሶኛል።
- 24
ስምዖንንም አወጣላቸው። ሰውዮውም እነዚያን ስዎች ወደ ዮሴፍ ቤት አስገባቸው፤ ውኃ አመጣላቸው፥ እግራቸውንም ታጠቡ፤ ለአህዮቻቸው አበቅ ሰጣቸው።
- 25
ዮሴፍም በእኩለ ቀን እስኪገባ ድረስ እነርሱ እጅ መንሻቸውን አዘጋጁ፥ ከዚያ እንጀራን እንደሚበሉ ሰምተዋልና።
- 26
ዮሴፍም ወደ ቤቱ በገባ ጊዜ በእጃቸው ያለውን እጅ መንሻ በቤት ውስጥ አቀረቡለት፥ ወደ ምድርም ወድቀው ሰገዱለት።
- 27
እርሱም ደኅንነታቸውን ጠየቃቸው፥ እንዲህም አለ። የነገራችሁኝ ሽማግሌ አባታችሁ ደኅና ነውን? ገና በሕይወት አለን?
- 28
እነርሱም አሉት። ባሪያህ አባታችን ደኅና ነው፤ ገና በሕይወት አለ። አጐንብሰውም ሰገዱለት።
- 29
ዓይኑንም አንሥቶ የእናቱን ልጅ ብንያምን አየው፥ እርሱም አለ። የነገራችሁኝ ታናሽ ወንድማችሁ ይህ ነውን? እንዲህም አለው። ልጄ ሆይ፥ እግዚአብሔር ይባርክህ።
- 30
ዮሴፍም ቸኮለ፥ አንጀቱ ወንድሙን ናፍቆታልና፤ ሊያለቅስም ወደደ፤ ወደ እልፍኙም ገብቶ ከዚያ አለቀሰ።
- 31
ፊቱንም ታጥቦ ወጣ፥ ልቡንም አስታግሦ። እንጀራ አቅርቡ አለ።
- 32
ለእርሱም ለብቻው አቀረቡ፥ ለእነርሱም ለብቻቸው፥ ከእርሱ ጋር ለሚበሉት ለግብፅ ሰዎችም ለብቻቸው፤ የግብፅ ሰዎች ከዕብራውያን ጋር መብላት አይሆንላቸውምና፥ ይህ ለግብፅ ሰዎች እንደ መርከስ ነውና።
- 33
በፊቱም በኵሩ እንደ ታላቅነቱ ታናሹም እንደ ታናሽነቱ ተቀመጡ፤ ሰዎቹም እርስ በርሳቸው ተደነቁ።
- 34
በፊቱም ካለው መብል ፈንታቸውን አቀረበላቸው፤ የብንያምም ፈንታ ከሁሉ አምስት እጅ የሚበልጥ ነበረ። እነርሱም ጠጡ ከእርሱም ጋር ደስ አላቸው።