Genesis 39
World English Bible (en) → Amharic Bible (am)
- 1
ዮሴፍ ግን ወደ ግብፅ ወረደ፤ የፈርዖን ጃንደረባ የዘበኞቹም አለቃ የሚሆን የግብፅ ሰው ጲጥፋራ ወደ ግብፅ ካወረዱት ከእስማኤላውያን እጅ ገዛው።
- 2
እግዚአብሔር ከዮሴፍ ጋር ነበረ፥ ሥራውም የተከናወነለት ሰው ሆነ፤ በግብፃዊው ጌታውም ቤት ነበረ።
- 3
ጌታውም እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር እንዳለ፥ እርሱ የሚሠራውንም ሁሉ እግዚአብሔር በእጁ እንዲያከናውንለት አየ።
- 4
ዮሴፍም በጌታው ፊት ሞገስን አገኘ፥ እርሱንም ያገለግለው ነበር፤ በቤቱም ላይ ሾመው፥ ያለውንም ሁሉ በእጁ ሰጠው።
- 5
እንዲህም ሆነ፤ በቤቱ ባለውም ሁሉ ላይ ከሾመው በኋላ እግዚአብሔር የግብፃዊውን ቤት ስለ ዮሴፍ ባረከው፤ የእግዚአብሔር በረከት በውጪም በግቢም ባለው ሁሉ ላይ ሆነ።
- 6
ያለውንም ሁሉ ለዮሴፍ አስረከበ፤ ከሚበላውም እንጀራ በቀር ምንም የሚያውቀው አልነበረም። የዮሴፍም ፊቱ መልከ መልካምና ውብ ነበረ።
- 7
ከዚህም በኋላ እንዲህ ሆነ፤ የጌታው ሚስት በዮሴፍ ላይ ዓይንዋን ጣለች። ከእኔም ጋር ተኛ አለችው።
- 8
እርሱም እንቢ አለ፥ ለጌታውም ሚስት እንዲህ አላት። እነሆ ጌታዬ በቤቱ ያለውን ምንም ምን የሚያውቀው የለም፥ ያለውንም ሁሉ ለእኔ አስረክቦኛል፤
- 9
ለዚህ ቤት ከእኔ የሚበልጥ ሰው የለም፤ ሚስቱ ስለ ሆንሽ ከአንቺም በቀር ያልሰጠኝ ነገር የለም፤ እንዴት ይህን ትልቅ ክፉ ነገር አደርጋለሁ? በእግዚአብሔር ፊት እንዴት ኃጢአትን እሠራለሁ?
- 10
ይህንም ነገር በየዕለቱ ለዮሴፍ ትነግረው ነበር፤ እርሱም ከእርስዋ ጋር ይተኛ ዘንድ ከእርስዋም ጋር ይሆን ዘንድ አልሰማትም።
- 11
እንዲህም ሆነ፤ በዚያን ጊዜ ሥራውን እንዲሠራ፤ ወደ ቤቱ ገባ፤ በቤትም ውስጥ ከቤት ሰዎች ማንም አልነበረም።
- 12
ከእኔ ጋር ተኛ ስትል ልብሱን ተጠማጥማ ያዘች፤ እርሱም ልብሱን በእጅዋ ትቶላት ሸሸ ወደ ውጭም ወጣ።
- 13
እንዲህም ሆነ፤ ልብሱን ትቶ ወደ ውጭ እንደ ሸሸ ባየች ጊዜ፥
- 14
የቤትዋን ሰዎች ወደ እርስዋ ጠርታ እንዲህ ብላ ነገረቻቸው። እዩ፤ ዕብራዊው ሰው በእኛ እንዲሣለቅ አግብቶብናል፤፤ እርሱ ከእኔ ጋር ሊተኛ ወደ እኔ ገባ፥ እኔም ድምፄን ከፍ አድርጌ ጮኽሁ፤
- 15
ድምፄንም ከፍ አድርጌ እንደ ጮኽሁ ቢሰማ ልብሱን በእኔ ዘንድ ጥሎ ሸሸ ወደ ውጭም ወጣ።
- 16
ጌታው ወደ ቤቱ እስኪገባ ድረስም ልብሱን ከእርስዋ ዘንድ አኖረች።
- 17
ይህንም ነገር እንዲህ ብላ ነገረችው። ያገባህልን ዕብራዊው ባሪያ ሊሣለቅብኝ ወደ እኔ ገባ፤
- 18
እኔም ድምፄን ከፍ አድርጌ ስጮኽ ልብሱን በእጄ ተወና ወደ ውጭ ሸሸ።
- 19
ጌታውም። ባሪያህ እንዲህ አደረገኝ ብላ የነገረችውን የሚስቱን ቃል በሰማ ጊዜ እጅግ ተቆጣ።
- 20
የዮሴፍም ጌታ ወሰደው፥ የንጉሡ እስረኞችም ወደሚታሰሩበት ስፍራ ወደ ግዞት ቤት አገባው፤ ከዚያም በግዞት ነበረ።
- 21
እግዚአብሔርም ከዮሴፍ ጋር ነበረ ምሕረትንም አበዛለት፥ በግዞት ቤቱም አለቃ ፊት ሞገስን ሰጠው።
- 22
የግዞት ቤቱም አለቃ በግዞት ያሉትን እስረኞች ሁሉ በዮሴፍ እጅ አሳልፎ ሰጣቸው፤ በዚያም የሚደረገው ነገር ሁሉ እርሱ የሚያደርገው ነበረ።
- 23
የግዞት ቤቱም አለቃ በእጁ ያለውን ነገር ከቶ አላሰበም፥ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ነበረና፤ የሚያደርገውንም ሁሉ እግዚአብሔር ያቀናለት ነበር።