Exodus 9
World English Bible (en) → Amharic Bible (am)
- 1
እግዚአብሔርም ሙሴን አለው። ወደ ፈርዖን ዘንድ ገብተህ ንገረው። የዕብራውያን አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ያገለግሉኝ ዘንድ ሕዝቤን ልቀቅ።
- 2
ልትለቅቃቸውም እንቢ ብትል ብትይዛቸውም፥
- 3
እነሆ የእግዚአብሔር እጅ በሜዳ ውስጥ ባሉት በከብቶችህ፥ በፈረሶችም በአህዮችም በግመሎችም በበሬዎችም በበጎችም ላይ ትሆናለች፤ ብርቱ ቸነፈርም ይወርዳል።
- 4
እግዚአብሔርም በእስራኤልና በግብፅ ከብቶች መካከል ይለያል፤ ከእስራኤልም ልጆች ከብት አንዳች አይጠፋም።
- 5
እግዚአብሔርም። ነገ እግዚአብሔር ይህን ነገር በምድር ላይ ያደርጋል ብሎ ጊዜን ወሰነ።
- 6
እግዚአብሔርም ያንን ነገር በነጋው አደረገ፥ የግብፅም ከብት ሁሉ ሞተ፤ ከእስራኤል ልጆች ከብት ግን አንድ ስንኳ አልሞተም።
- 7
ፈርዖንም ላከ፥ እነሆም ከእስራኤል ልጆች ከብት አንድ ስንኳ አልሞተም። የፈርዖን ልብ ግን ደነደነ፥ ሕዝቡንም አልለቀቀም።
- 8
እግዚአብሔርም ሙሴንና አሮንን። እጃችሁን ሞልታችሁ ከምድጃ አመድ ውሰዱ፥ ሙሴም በፈርዖን ፊት ወደ ሰማይ ይበትነው።
- 9
እርሱም በግብፅ አገር ሁሉ ትቢያ ይሆናል፥ በግብፅም አገር ሁሉ በሰውና በእንስሳ ላይ ሻህኝ የሚያመጣ ቍስል ይሆናል አላቸው።
- 10
ከምድጃውም አመድ ወስደው በፈርዖን ፊት ቆሙ፤ ሙሴም ወደ ሰማይ በተነው፥ በሰውና በእንስሳም ላይ ሻህኝ የሚያወጣ ቍስል ሆነ።
- 11
ጠንቋዮችም ቍስል ስለ ነበረባቸው በሙሴ ፊት መቆም አልቻሉም፤ ቍስል በጠንቋዮችና በግብፃያን ሁሉ ላይ ነበረና።
- 12
እግዚአብሔርም የፈርዖንን ልብ አጸና፤ እግዚአብሔር ለሙሴ እንደተናገረው አልሰማቸውም።
- 13
እግዚአብሔርም ሙሴን አለው። ማልደህ ተነሣ፥ በፈርኦንም ፊት ቆመህ በለው። የዕብራውያን አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እንዲያገለግሉኝ ሕዝቤን ልቀቅ።
- 14
በምድር ሁሉ እንደ እኔ ያለ እንደሌለ ታውቅ ዘንድ በሰውነትህ በባሪያዎችህም በሕዝብህም ላይ መቅሠፍቴን ሁሉ አሁን እልካለሁ።
- 15
አሁን እጄን ዘርግቼ አንተን ሕዝብህንም በቸነፈር በመታሁህ ነበር፥ አንተም ከምድር በጠፋህ ነበር፤
- 16
ነገር ግን ኃይሌን እገልጥብህ ዘንድ ስሜም በምድር ሁሉ ላይ ይነገር ዘንድ ስለዚህ አስነሥቼሃለሁ።
- 17
እንዳትለቅቃቸው ገና በሕዝቤ ላይ ትታበያለህን?
- 18
እነሆ ነገ በዚህ ጊዜ፥ ከተመሰረተች ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ እንደ እርሱ ያለ በግብፅ ሆኖ የማያውቅ፥ እጅግ ታላቅ በረዶ አዘንብብሃለሁ።
- 19
በሜዳ የተገኘ ወደ ቤት ያልገባ ሰውና እንስሳ ሁሉ በረዶ ወርዶበት ይሞታልና አሁን እንግዲህ ላክ፥ ከብቶችህንም በሜዳም ያለህን ሁሉ አስቸኵል።
- 20
ከፈርዖንም ባሪያዎች የእግዚአብሔርን ቃል የፈራ ባሪያዎቹንና ከብቶቹን ወደ ቤቶቹ አሸሸ፤
- 21
የእግዚአብሔርንም ቃል ያላሰበ ባሪያዎቹንና ከብቶቹን በሜዳ ተወ።
- 22
እግዚአብሔርም ሙሴን። በግብፅ አገር በሰው በእንስሳም በእርሻም ቡቃያ ሁሉ ላይ፥ በግብፅ አገር ሁሉ በረዶ ይሆን ዘንድ እጅህን ወደ ሰማይ ዘርጋ አለው።
- 23
ሙሴም በትሩን ወደ ሰማይ ዘረጋ፤ እግዚአብሔርም ነጎድጓድና በረዶ ላከ፥ እሳትም ወደ ምድር ወረደ፤ እግዚአብሔርም በግብፅ አገር ላይ በረዶ አዘነበ።
- 24
በረዶም ነበረ፥ በበረዶውም መካከል እሳት ይቃጠል ነበር፥ በረዶውም በግብፅ አገር ሁሉ ሕዝብ ከሆነ ጀምሮ እንደ እርሱ ያልሆነ እጅግ ታላቅ ነበረ።
- 25
በረዶውም በግብፅ አገር ሁሉ በሜዳ ያለውን ሁሉ ሰውንና እንስሳን መታ፤ በረዶውም የእርሻን ቡቃያ ሁሉ መታ፥ የአገሩንም ዛፍ ሁሉ ሰበረ።
- 26
የእስራኤል ልጆች ተቀምጠው በነበሩባት በጌሤም አገር ብቻ በረዶ አልወረደም።
- 27
ፈርዖንም ልኮ ሙሴንና አሮንን ጠራ። በዚህ ጊዜ በደልሁ፤ እግዚአብሔር ጻድቅ ነው፥ እኔና ሕዝቤም ኃጢያተኞች ነን።
- 28
የአምላክ ነጎድጓድ በረዶውም በዝቶአልና ወደ እግዚአብሔር ጸልዩ፤ እለቅቃችሁማለሁ፥ ከዚያም በኋላ በዚህ አትቀመጡም አላቸው።
- 29
ሙሴም። ከከተማ በወጣሁ ጊዜ እጄን ወደ እግዚአብሔር እዘረጋለሁ፤ ምድሪቱ ለእግዚአብሔር እንደሆነች ታውቅ ዘንድ ነጎድጓዱ ይቀራል፥ በረዶውም ደግሞ አይወርድም።
- 30
ነገር ግን አንተና ባሪያዎችህ አምላክን እግዚአብሔርን ገና እንደማትፈሩ አውቃለሁ አለው።
- 31
ገብሱ እሸቶ ተልባውም ኣፍርቶ ነበርና ተልባና ገብሱ ተመታ።
- 32
ስንዴውና አጃው ግን ጊዜው ገና ነበርና አልተመታም።
- 33
ሙሴም ከፈርዖን ዘንድ ከከተማ ወጣ፥ እጁንም ወደ እግዚአብሔር ዘረጋ፤ ነጎድጓዱም በረዶውም ተቋረጠ፥ ዝናቡም በምድር ላይ አልፈሰሰም።
- 34
ፈርዖንም ዝናቡ በረዶውም ነጎድጓዱም እንደ ተቋረጠ ባየ ጊዜ ኃጢያትን ጨመረ፥ እርሱና ባሪያዎቹም ልባቸውን አደነደኑ።
- 35
የፈርዖንም ልብ ጸና፤ እግዚአብሔርም በሙሴ አፍ እንደተናገር የእስራኤልን ልጆች አልለቀቀም።