Exodus 37
World English Bible (en) → Amharic Bible (am)
- 1
ባስልኤልም ከግራር እንጨት ታቦቱን ሠራ፤ ርዝመቱም ሁለት ክንድ ተኩል፥ ወርዱም አንድ ክንድ ተኩል፥ ቁመቱም አንድ ክንድ ተኩል ነበረ።
- 2
በውስጥም በውጭም በጥሩ ወርቅ ለበጠው፤ በዙሪያውም የወርቅ አክሊል አደረገለት።
- 3
አራት የወርቅ ቀለበቶችም አደረገለት፤ እነርሱንም በአራቱ እግሮቹ ላይ አኖረ። በአንድ ወገን ሁለት ቀለበቶች፥ በሌላውም ወገን ሁለት ቀለበቶች ሆኑ።
- 4
መሎጊያዎቹንም ከግራር እንጨት ሠራ፥ በወርቅም ለበጣቸው።
- 5
ታቦቱንም ለመሸከም በታቦቱ አጠገብ ባሉት ቀለበቶች መሎጊያዎቹን አገባ።
- 6
ከጥሩ ወርቅም ርዝመቱ ሁለት ክንድ ተኩል፥ ወርዱም አንድ ክንድ ተኩል የሆነ የስርየት መክደኛ ሠራ።
- 7
ሁለት ኪሩቤልንም ከተቀጠቀጠ ወርቅ ሠራ፤ በስርየት መክደኛውም ላይ በሁለት ወገን አደረጋቸው።
- 8
ከስርየት መክደኛውም ጋር አንዱን ኪሩብ በአንድ ወገን፥ ሁለተኛውንም ኪሩብ በሌላው ወገን አድርጎ በአንድ ላይ ሠራቸው።
- 9
ኪሩቤልም ክንፎቻቸውን ወደ ላይ የዘረጉ ሆኑ፥ የስርየት መክደኛውንም በክንፎቻቸው ሸፈኑ፥ እርስ በርሳቸውም ተያዩ፤ የኪሩቤልም ፊቶቻቸው ወደ መክደኛው ተመለከቱ።
- 10
ርዝመቱ ሁለት ክንድ፥ ወርዱም አንድ ክንድ፥ ቁመቱም አንድ ክንድ ተኩል የሆነውን ገበታ ከግራር እንጨት ሠራ።
- 11
በጥሩም ወርቅ ለበጠው፥ በዙሪያውም የወርቅ አክሊል አደረገለት።
- 12
በዙሪያውም አንድ ጋት የሚያህል ክፈፍ አደረገለት፤ የወርቅም አክሊል በክፈፉ ዙሪያ አደረገለት።
- 13
አራትም የወርቅ ቀለበቶች አደረገለት፤ ቀለበቶቹንም አራቱ እግሮቹ ባሉበት በአራቱ ማዕዘኖች አደረገ።
- 14
ገበታውንም ለመሸከም መሎጊያዎቹ እንዲሰኩባቸው ቀለበቶች በክፈፉ አቅራቢያ ነበሩ።
- 15
ገበታውንም ይሸከሙባቸው ዘንድ መሎጊያዎቹን ከግራር እንጨት ሠርቶ በወርቅ ለበጣቸው።
- 16
ለማፍሰሻም ይሆኑ ዘንድ በገበታው ላይ የሚኖሩትን ዕቃዎች፥ ወጭቶቹንና ጭልፋዎቹን ጽዋዎቹንም መቅጃዎቹንም፥ ከጥሩ ወርቅ አደረጋቸው።
- 17
መቅረዙንም ከጥሩ ወርቅ አደረገ፤ መቅረዙንም ከእግሩና ከአገዳው ጋር በተቀረጸ ሥራ አደረገ፤ ጽዋዎቹን፥ ጕብጕቦቹን፥ አበቦቹን ከዚያው በአንድነት አደረገ።
- 18
በስተ ጎኑም ስድስት ቅርንጫፎች ወጡለት፤ ሦስቱ የመቅረዙ ቅርንጫፎች በአንድ ወገን፥ ሦስቱም የመቅረዙ ቅርንጫፎች በሌላ ወገን ወጡ።
- 19
በአንደኛው ቅርንጫፍ ጕብጕቡንና አበባውን ሦስትም የለውዝ አበባ የሚመስሉትን ጽዋዎች፥ በሁለተኛውም ቅርንጫፍ ጕብጕቡንና አበባውን ሦስትም የለውዝ አበባ የሚመስሉትን ጽዋዎች፥ እንዲሁም ከመቅረዙ ለወጡ ለስድስቱ ቅርንጫፎች አደረገ።
- 20
በመቅረዙም ጕብጕቦቹንና አበቦቹን አራትም የለውዝ አበባ የሚመስሉትን ጽዋዎች አደረገ።
- 21
ከመቅረዙ ለወጡ ለስድስት ቅርንጫፎች ከሁለት ቅርንጫፎች በታች አንድ ሆኖ የተሠራ አንድ ጕብጕብ፥ ከሁለትም ቅርንጫፎች በታች አንድ ሆኖ የተሠራ አንድ ጕብጕብ፥ ደግሞ ከሁለት ቅርንጫፎች በታች አንድ ሆኖ የተሠራ አንድ ጕብጕብ ነበረ።
- 22
ጕብጕቦቹና ቅርንጫፎቹ ከእርሱ ጋር አንድ ነበሩ፤ ሁሉም አንድ ሆኖ ከተቀረጸ ከጥሩ ወርቅ ተሠርቶ ነበር።
- 23
ሰባቱንም መብራቶች መኰስተሪያዎቹንም፥ የኩስታሪ ማድረጊያዎቹንም ከጥሩ ወርቅ ሠራ።
- 24
መቅረዙንም ዕቃውንም ሁሉ ከአንድ መክሊት ጥሩ ወርቅ አደረገ።
- 25
የዕጣን መሠዊያ ከግራር እንጨት ሠራ፤ ርዝመቱ አንድ ክንድ፥ ስፋቱ አንድ ክንድ፥ አራት ማዕዘን ነበረ፤ ከፍታውም ሁለት ክንድ ነበረ፤ ቀንዶቹም ከእርሱ ጋር በአንድነት የተሠሩ ነበሩ።
- 26
ላይኛውንና የግድግዳውንም ዙሪያ ቀንዶቹንም በጥሩ ወርቅ ለበጠው፤ በዙሪያውም የወርቅ ክፈፍ አደረገበት።
- 27
ከክፈፉም በታች ሁለት የወርቅ ቀለበቶች አደረገበት፥ በዚህና በዚያ በሁለቱም ጎን አደረጋቸው፤ ለመሸከምም የመሎጊያዎች ስፍራ ነበሩ።
- 28
መሎጊያዎቹንም ከግራር እንጨት አደረገ፥ በወርቅም ለበጣቸው።
- 29
የተቀደሰውንም የቅብዓቱን ዘይት፥ ጥሩውንም የጣፋጭ ሽቱ ዕጣን በቀማሚ ብልሃት እንደ ተሠራ አደረገ።