Ecclesiastes 8
World English Bible (en) → Amharic Bible (am)
- 1
እንደ ጠቢብ የሆነ ሰው ማን ነው? ነገርንስ መተርጐም የሚያውቅ ማን ነው? የሰው ጥበብ ፊቱን ታበራለች፥ የፊቱንም ድፍረት ትለውጣለች።
- 2
እኔ። በእግዚአብሔር መሐላ ምክንያት የንጉሥን ትእዛዝ ጠብቅ እልሃለሁ።
- 3
የወደደውን ሁሉ ያደርጋልና ከፊቱ ትወገድ ዘንድ አትቸኵል፥ ክፉንም በማድረግ አትጽና።
- 4
የንጉሥ ቃል ኃይለኛ ነውና፤ ይህንስ ለምን ታደርጋለህ? ማን ይለዋል?
- 5
ትእዛዝን የሚጠብቅ ክፉን ነገር አያውቅም፤ የጠቢብም ልብ ጊዜንና ፍርድን ያውቃል።
- 6
የሰው መከራ በእርሱ ላይ እጅግ ስለ ሆነ ለነገር ሁሉ ጊዜና ፍርድ አለውና።
- 7
የሚሆነውንም አያውቅም፤ እንዴትስ እንደሚሆን የሚነግረው ማን ነው?
- 8
መንፈስን ለማስቀረት በመንፈስ ላይ ሥልጣን ያለው ሰው የለም፤ በሞቱም ቀን ሥልጣን የለውም፤ በሰልፍም ስንብቻ የለም፥ ኃጢአትም ሠሪውን አያድነውም።
- 9
ይህን ሁሉ አየሁ፥ ከፀሐይም በታች ወደ ተደረገው ሥራ ሁሉ ልቤን ሰጠሁ፤ ሰው ሰውን ለመጕዳት ገዢ የሚሆንበት ጊዜ አለ።
- 10
እንዲሁም ኀጥኣን ተቀብረው አየሁ፥ ወደ ዕረፍትም ገቡ፤ ነገር ግን ቅን አድራጊዎች ከቅድስት ስፍራ ወጡ፥ በከተማይቱም ውስጥ ተረሱ፤ ይህም ደግሞ ከንቱ ነው።
- 11
በክፉ ሥራ ላይ ፈጥኖ ፍርድ አይፈረድምና ስለዚህ በሰው ልጆች ውስጥ ልባቸው ክፉን ለመሥራት ጠነከረ።
- 12
ኃጢአተኛ መቶ ጊዜ ክፉን ቢሠራ ዘመኑም ረጅም ቢሆን፥ እግዚአብሔርን ለሚፈሩት በፊቱም ለሚፈሩት ደኅንነት እንዲሆን አውቃለሁ፤
- 13
ለኀጥእ ግን ደኅንነት የለውም፥ በእግዚአብሔርም ፊት አይፈራምና ዘመኑ እንደ ጥላ አትረዝምም።
- 14
በምድር የሚደረግ ከንቱ ነገር አለ፤ በኀጥኣን የሚደረገው ሥራ የሚደርስባቸው ጻድቃን አሉ፥ ለጻድቃንም የሚደረገው ሥራ የሚደርስላቸው ኀጥኣን አሉ፤ ይህም ደግሞ ከንቱ ነው አልሁ።
- 15
ከሚበላውና ከሚጠጣው ደስም ከሚለው በቀር ለሰው ከፀሐይ በታች ሌላ መልካም ነገር የለውምና እኔ ደስታን አመሰገንሁ፤ ከፀሐይም በታች ከድካሙ እግዚአብሔር በሰጠው በሕይወቱ ዘመን ይህ ደስታው ከእርሱ ጋር ይኖራል።
- 16
ጥበብን አውቅ ዘንድ በምድር የሚሆነውንም ድካም አይ ዘንድ ልቤን ሰጠሁ፥ በቀንና በሌሊት እንቅልፍን በዓይኑ የማያይ አለና፤
- 17
ከፀሐይም በታች የተደረገውን ሥራ መርምሮ ያገኝ ዘንድ ለሰው እንዳይቻለው የእግዚአብሔርን ሥራ ሁሉ አየሁ። ሰውም ሊፈልግ እጅግ ቢደክም መርምሮ አያገኘውም፤ ደግሞ ጠቢብ ሰው። ይህን አወቅሁ ቢል እርሱ ያኘው ዘንድ አይችልም።