Deuteronomy 3
World English Bible (en) → Amharic Bible (am)
- 1
ተመልሰን በባሳን መንገድ ወጣን፥ የባሳን ንጉሥ ዐግም ሕዝቡም ሁሉ በኤድራይ ሊዋጉን ወጡ።
- 2
እግዚአብሔርም። እርሱንና ሕዝቡን ሁሉ ምድሩንም በእጅህ አሳልፌ ሰጥቼአለሁና አትፍራው፤ በሐሴቦን ይኖር በነበረው በአሞራውያን ንጉሥ በሴዎን ላይ እንዳደረግህ በእርሱም ታደርግበታለህ አለኝ።
- 3
አምላካችን እግዚአብሔርም ደግሞ የባሳንን ንጉሥ ዐግን ሕዝቡንም ሁሉ በእጃችን አሳልፎ ሰጠን፤ እኛም መታነው፤ አንድ ሰው እንኳ አምልጦ አልቀረለትም።
- 4
በዚያን ጊዜም ከተሞቹን ሁሉ ወሰድን፤ አንድም ያልወሰድነው የለም፤ በባሳን ያለውን የዐግን መንግሥት፥ የአርጎብን አገር ሁሉ፥ ስድሳ ከተሞችን ወሰድን።
- 5
በቅጥር ካልተመሸጉት ከእጅግ ብዙ ከተሞች ሌላ፥ እነዚህ ከተሞች ሁሉ ቁመቱ ረጅም በሆነ ቅጥር በመዝጊያና በመወርወሪያም የተመሸጉ ነበሩ።
- 6
በሐሴቦንም ንጉሥ በሴዎን እንዳደረግን ፈጽሞ አጠፋናቸው፤ ከተሞቹን ሁሉ ከወንዶችና ከሴቶች ከሕፃናቶችም ጋር አጠፋናቸው።
- 7
ከብቶቹን ሁሉ የከተሞቹንም ምርኮ ለእኛ በዘበዝን።
- 8
በዚያም ዘመን ከአርኖን ሸለቆ ጀምሮ እስከ አርሞንዔም ተራራ ድረስ ምድሪቱን በዮርዳኖስ ማዶ ከነበሩ ከሁለቱ ከአሞራውያን ነገሥታት እጅ ወሰድን፤
- 9
ሲዶናውያን አርሞንዔምን ሢርዮን ብለው ይጠሩታል፥ አሞራውያንም ሳኔር ብለው ይጠሩታል።
- 10
በሜዳውም ያሉትን ከተሞች ሁሉ፥ ገለዓድንም ሁሉ፥ በባሳንም ያሉትን የዐግን መንግሥት ከተሞች እስከ ሰልካና እስከ ኤድራይ ድረስ ባሳንን ሁሉ ወሰድን።
- 11
ከራፋይም ወገን የባሳን ንጉሥ ዐግ ብቻውን ቀርቶ ነበር፤ እነሆ፥ አልጋው የብረት አልጋ ነበረ፤ እርሱ በአሞን ልጆች አገር በነበረባት አለ፤ ርዝመቱ ዘጠኝ ክንድ ወርዱም አራት ክንድ በሰው ክንድ ልክ ነበረ።
- 12
ይህችንም ምድር በዚያን ዘመን ወረስን፤ በአርኖንም ሸለቆ አጠገብ ካለችው ከአሮዔር ጀምሮ የገለዓድን ተራራማ አገር እኩሌታ ከተሞቹንም ለሮቤልና ለጋድ ነገድ ሰጠኋቸው።
- 13
ከገለዓድም የቀረውን የዐግንም መንግሥት ባሳንን ሁሉ፥ የአርጎብንም ምድር ሁሉ ለምናሴ ነገድ እኩሌታ ሰጠሁ፤ ያችም ባሳን ሁሉ የራፋይም አገር ተብላ ተቈጠረች።
- 14
የምናሴ ልጅ ኢያዕር እስከ ጌሹራውያንና እስከ ማዕካታውያን ዳርቻ ድረስ የአርጎብን ምድር ሁሉ ወሰደ፤ ይህችንም የባሳንን ምድር እስከ ዛሬ ድረስ በስሙ የኢያዕር መንደሮች ብሎ ጠራ።
- 15
ለማኪርም ገልዓድን ሰጠሁት።
- 16
ለሮቤል ነገድና ለጋድም ነገድ ከገለዓድ ጀምሮ እስከ አርኖን ሸለቆ ድረስ የሸለቆውን እኩሌታ ዳርቻውንም፥ እስከ አሞን ልጆች ዳርቻ እስከ ያቦቅ ወንዝ ድረስ፥
- 17
ከኪኔሬት እስከ ዓረባ ባሕር እርሱም የጨው ባሕር ድረስ ከፈስጋ ተራራ በታች ወደ ምሥራቅ ያለውን ዓረባ ዮርዳኖስንም ዳሩንም ሰጠኋቸው።
- 18
በዚያም ዘመን እንዲህ ብዬ አዘዝኋችሁ። አምላካችሁ እግዚአብሔር ይህችን ምድር ርስት አድርጎ ሰጥቶአችኋል፤ መሣሪያችሁን ይዛችሁ እናንተ አርበኞች ሁሉ በወንድሞቻችሁ በእስራኤል ልጆች ፊት ትሻገራላችሁ።
- 19
ነገር ግን እጅግ ከብቶች እንዳሉአችሁ አውቃለሁና ሴቶቻችሁና ልጆቻችሁ ከብቶቻችሁም በሰጠኋችሁ ከተሞች ይቀመጣሉ፤
- 20
ይኸውም እግዚአብሔር እናንተን እንዳሳረፈ፥ ወንድሞቻችሁን እስኪያሳርፍ ድረስ እነርሱም ደግሞ በዮርዳኖስ ማዶ አምላካችሁ እግዚአብሔር የሚሰጣቸውን ምድር እስኪወርሱ ድረስ ነው፤ ከዚያም በኋላ እናንተ ሁሉ ወደ ሰጠኋችሁ ርስት ትመለሳላችሁ።
- 21
በዚያም ጊዜ ኢያሱን። አምላካችሁ እግዚአብሔር በእነዚህ በሁለቱ ነገሥት ያደረገውን ሁሉ ዓይኖችህ አይተዋል፤ እንዲሁ በምታልፍባቸው መንግሥታት ሁሉ ላይ እግዚአብሔር ያደርጋል።
- 22
አምላካችሁ እግዚአብሔር እርሱ ስለ እናንተ ይዋጋልና አትፍራቸውም ብዬ አዘዝሁት።
- 23
በዚያም ዘመን እኔ ወደ እግዚአብሔር እንዲህ ብዬ ለመንሁ።
- 24
ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፥ ታላቅነትህን የጸናችውንም እጅህን ለእኔ ለባሪያህ ማሳየት ጀምረሃል፤ በሰማይና በምድርም እንደ ሥራህ እንደ ኃይልህም ይሠራ ዘንድ የሚችል አምላክ ማን ነው?
- 25
እኔ ልሻገር በዮርዳኖስም ማዶ ያለችውን መልካሚቱን ምድር ያንም መልካሙን ተራራማውን አገር ሊባኖስንም ልይ።
- 26
እግዚአብሔር ግን በእናንተ ምክንያት ተቈጣኝ አልሰማኝምም፤ እግዚአብሔርም አለኝ። ይበቃሃል፤ በዚህ ነገር ደግመህ አትናገረኝ።
- 27
ይህን ዮርዳኖስን አትሻገርምና ወደ ፈስጋ ራስ ውጣ፤ ዓይንህንም ወደ ምዕራብ ወደ ሰሜንም ወደ ደቡብም ወደ ምሥራቅም አንሥተህ በዓይንህ ተመልከት።
- 28
ኢያሱ በዚህ ሕዝብ ፊት ይሻገራልና፥ አንተም የምታያትን ምድር እርሱ ያወርሳቸዋልና ኢያሱን እዘዘው፥ አደፋፍረውም፥ አጽናውም።
- 29
በቤተፌጎርም ፊት ለፊት በሸለቆው ውስጥ ተቀመጥን።