2 Samuel 22
World English Bible (en) → Amharic Bible (am)
- 1
ዳዊትም እግዚአብሔር ከሳኦል እጅና ከጠላቶቹ እጅ ሁሉ ባዳነው ቀን የዚህን ቅኔ ቃል ለእግዚአብሔር ተናገረ።
- 2
እንዲህም አለ። እግዚአብሔር ዓለቴ አምባዬ መድኃኒቴ ነው፤
- 3
እግዚአብሔር ጠባቂዬ ነው፥ በእርሱም እታመናለሁ፤ ጋሻዬና የረድኤቴ ቀንድ፥ መጠጊያዬና መሸሸጊያዬ፥ መድኃኒቴ ሆይ፥ ከግፍ ሥራ ታድነኛለህ።
- 4
ምስጋና የሚገባውን እግዚአብሔርን እጠራለሁ፤ ከጠላቶቼም እድናለሁ።
- 5
የሞት ጣር ያዘኝ፤ የዓመፅ ፈሳሽም አስፈራኝ፤
- 6
የሲኦል ጣር ከበበኝ፤ የሞት ወጥመድ ደረሰብኝ።
- 7
በጨነቀኝ ጊዜ እግዚአብሔርን ጠራሁት፥ ወደ አምላኬም ጮኽሁ፤ ከመቅደሱም ቃሌን ሰማኝ፥ ጩኸቴም በፊቱ ወደ ጆሮው ገባ።
- 8
ምድርም ተንቀጠቀጠች፥ ተናወጠችም፥ የሰማዮችም መሠረቶች ተነቃነቁ፤ እግዚአብሔርም ተቈጥቶአልና ተንቀጠቀጡ።
- 9
ከቍጣው ጢስ ወጣ፥ ከአፉም የሚበላ እሳት ነደደ፤ ፍምም ከእርሱ በራ።
- 10
ሰማዮችን ዝቅ ዝቅ አደረገ፥ ወረደም፤ ጨለማም ከእግሩ በታች ነበረ።
- 11
በኪሩብም ላይ ተቀምጦ በረረ፤ በነፋስም ክንፍ ሆኖ ታየ፤
- 12
መሰወርያውን ጨለማ፥ በዙሪያውም የነበረውን ድንኳን፥ በደመና ውስጥ የነበረ የጨለማ ውኃ አደረገ።
- 13
በፊቱም ካለው ብርሃን የተነሣ ፍም ተቃጠለ።
- 14
እግዚአብሔርም ከሰማያት አንጐደጐደ፥ ልዑልም ቃሉን ሰጠ፤
- 15
ፍላጻውን ላከ፥ በተናቸውም መብረቆችን ላከ፥ አወካቸውም።
- 16
ከእግዚአብሔር ዘለፋ፥ ከመዓቱም መንፈስ እስትንፋስ የተነሣ፥ የባሕር ፈሳሾች ታዩ፥ የዓለም መሠረቶችም ተገለጡ።
- 17
ከላይ ሰደደ፥ ወሰደኝም፤ ከብዙ ውኆችም አወጣኝ።
- 18
ከብርቱዎች ጠላቶቼ፥ ከሚጠሉኝም አዳነኝ፤ በርትተውብኝ ነበርና።
- 19
በመከራዬ ቀን ደረሱብኝ፤ እግዚአብሔር ግን ደገፋዬ ሆነ።
- 20
ወደ ሰፊ ስፍራም አወጣኝ፤ ወድዶኛልና አዳነኝ።
- 21
እግዚአብሔር እንደ ጽድቄ ይከፍለኛል፤ እንደ እጄ ንጽሕና ይመልስልኛል፤
- 22
የእግዚአብሔርን መንገድ ጠብቄአለሁና፥ በአምላኬም አላመፅሁምና።
- 23
ፍርዱ ሁሉ በፊቴ ነበረና፤ ከሥርዓቱም አልራቅሁምና።
- 24
በእርሱ ዘንድ ቅን ነበርሁ፥ ከኃጢአቴም ተጠበቅሁ።
- 25
እግዚአብሔርም እንደ ጽድቄ፥ እንደ እጄም ንጽሕና በዓይኖቹ ፊት መለሰልኝ።
- 26
ከቸር ሰው ጋር ቸር ሆነህ ትገኛለህ፤ ከቅን ሰው ጋር ቅን ሆነህ ትገኛለህ፤
- 27
ከንጹሕ ጋር ንጹሕ ሆነህ ትገኛለህ፤ ከጠማማም ጋር ጠማማ ሆነህ ትገኛለህ።
- 28
አንተ የተጠቃውን ሕዝብ ታድናለህና፤ የትዕቢተኞችን ዓይን ግን ታዋርዳለህ።
- 29
አቤቱ፥ አንተ መብራቴ ነህና፤ እግዚአብሔርም ጨለማዬን ያበራል።
- 30
በአንተ ኃይል በጭፍራ ላይ እሮጣለሁና፤ በአምላኬም ቅጥሩን እዘልላለሁና።
- 31
የአምላክ መንገድ ፍጹም ነው፤ የእግዚአብሔር ቃል የነጠረ ነው፤ በእርሱ ለሚታመኑት ሁሉ ጋሻ ነው።
- 32
ከእግዚአብሔር በቀር አምላክ ማን ነው? ከአምላካችንስ በቀር አምባ ማን ነው?
- 33
ኃይልን የሚያስታጥቀኝ፥ መንገዴንም የሚያቃና፥
- 34
እግሮቼን እንደ ብሆር እግሮች የሚያበረታ፥ በኮረብቶችም የሚያቆመኝ እግዚአብሔር ነው።
- 35
እጆቼን ሰልፍ ያስተምራል፤ በክንዴም የናስ ቀስት እገትራለሁ።
- 36
የማዳንህንም ጋሻ ሰጠኸኝ፤ ተግሣጽህም አሳደገኝ።
- 37
አረማመዴን በበታቼ አሰፋህ፥ እግሮቼም አልተንሸራተቱም።
- 38
ጠላቶቼን አሳድዳቸዋለሁ፥ አጠፋቸውማለሁ፤ እስካጠፋቸውም ድረስ አልመለስም።
- 39
አስጨንቃቸዋለሁ መቆምም አይችሉም፥ ከእግሬም በታች ይወድቃሉ።
- 40
ለሰልፍም ኃይልን ታስታጥቀኛለህ፤ በላዬ የቆሙትን በበታቼ ታስገዛቸዋለህ።
- 41
የጠላቶቼን ጀርባ ሰጠኸኝ፥ የሚጠሉኝንም አጠፋሃቸው።
- 42
ጮኹ፥ የሚረዳቸውም አልነበረም፤ ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፥ አልሰማቸውምም።
- 43
እንደ ምድር ትቢያ ፈጨኋቸው፤ እንደ አደባባይም ጭቃ ረገጥኋቸው፥ ደቀደቅኋቸውም።
- 44
ከሕዝብ ክርክር ታድነኛለህ፤ የአሕዛብም ራስ አድርገህ ትሾመኛለህ፤ የማላውቀው ሕዝብም ይገዛልኛል።
- 45
የባዕድ ልጆች ደለሉኝ፤ በጆሮ ሰምተው ተገዙልኝ።
- 46
የባዕድ ልጆች እየጠፉ ይሄዳሉ፤ ከተዘጉ ስፍሮች እየተንቀጠቀጡ ይወጣሉ።
- 47
እግዚአብሔር ሕያው ነው፥ ጠባቂዬም ቡሩክ ነው፤ የመድኃኒቴ ጠባቂ አምላኬ ከፍ ከፍ ይበል፤
- 48
በቀሌን የሚመልስልኝ አምላክ፥ አሕዛብን በበታቼ የሚያስገዛ፥
- 49
ከጠላቶቼ የሚያወጣኝ እርሱ ነው፤ በእኔም ላይ ከቆሙ ከፍ ከፍ ታደርገኛለህ፤ ከግፈኛ ሰው ታድነኛለህ።
- 50
አቤቱ፥ ስለዚህ በአሕዛብ ዘንድ አመሰግንሃለሁ፥ ለስምህም እዘምራለሁ።
- 51
የንጉሡን መድኃኒት ታላቅ ያደርጋል፤ ቸርነቱንም ለቀባው፥ ለዳዊትና ለዘሩ፥ ለዘላለም ይሰጣል።