2 Samuel 18
World English Bible (en) → Amharic Bible (am)
- 1
ዳዊትም ከእርሱ ጋር የነበሩትን ሕዝብ ቈጠረ፥ ሻለቆችንና የመቶ አለቆችንም ሾመላቸው።
- 2
ዳዊትም ሕዝቡን ከኢዮአብ እጅ በታች ሲሶውን፥ ከኢዮአብም ወንድም ከጽሩያ ልጅ ከአቢሳ እጅ በታች ሲሶውን፥ ከጌት ሰውም ከኢታይ እጅ በታች ሲሶውን ሰደደ። ንጉሡም ሕዝቡን። እኔ ደግሞ ከእናንተ ጋር እወጣለሁ አላቸው።
- 3
ሕዝቡ ግን። አትወጣም፤ ብንሸሽ ስለ እኛ አያስቡም፤ ከእኛም እኩሌታው ቢሞት ስለ እኛ አያስቡም፤ አንተ ግን ለብቻህ ከእኛ ከአስሩ ሺህ ይልቅ ትበልጣለህ፤ አሁንም በከተማ ተቀምጠህ ብትረዳን ይሻላል አሉ።
- 4
ንጉሡም። መልካም የሚመስላችሁን አደርጋለሁ አላቸው። ንጉሡም በበሩ አጠገብ ቆመ፥ ሕዝቡም ሁሉ መቶ በመቶ ሺህ በሺህ እየሆኑ ወጡ።
- 5
ንጉሡም እዮአብንና አቢሳን ኢታይንም። ለብላቴናው ለአቤሴሎም ስለ እኔ ራሩለት ብሎ አዘዛቸው። ንጉሡም ስለአቤሴሎም አለቆቹን ሁሉ ሲያዝዝ ሕዝቡ ሁሉ ሰማ።
- 6
ሕዝቡም በእስራኤል ላይ ወደ ሜዳ ወጣ፤ ሰልፉም በኤፍሬም ሁሉ ውስጥ ሆነ።
- 7
በዚያም የእስራኤል ሕዝብ በዳዊት ባሪያዎች ፊት ተመቱ፥ በዚያም ቀን ታላቅ ውጊያ በዚያ ሆነ፥ ሃያ ሺህ ሰውም ሞተ።
- 8
ከዚያም ሰልፉ በአገሩ ሁሉ ፊት ላይ ተበተነ፤ በዚያም ቀን ሰይፍ ከዋጠው ሕዝብ ሁሉ ይልቅ ዱር ብዙ ዋጠ።
- 9
አቤሴሎም ከዳዊት ባሪያዎች ጋር በድንገት ተገናኘ፤ አቤሴሎምም በበቅሎ ተቀምጦ ነበር፥ በቅሎውም ብዙ ቅርንጫፍ ባለው በታላቅ ዛፍ በታች ገባ፥ ራሱም በዛፉ ተያዘ፤ በሰማይና በምድር መካከል ተንጠለጠለ፥ ተቀምጦበትም የነበረ በቅሎ አለፈ።
- 10
አንድ ሰውም አይቶ። እነሆ፥ አቤሴሎም በትልቅ ዛፍ ላይ ተንጠልጥሎ አየሁ ብሎ ለኢዮአብ ነገረው።
- 11
ኢዮአብም ለነገረው ሰው። እነሆ፥ ካየኸው ለምን ወደ ምድር አልመታኸውም? አስር ብርና አንድ ድግ እሰጥህ ነበር አለው።
- 12
ሰውዮውም ኢዮአብን። እኛ ስንሰማ ንጉሡ አንተንና አቢሳን ኢታይንም። ብላቴናውን አቤሴሎምን ማንም እንዳይነካው ተጠንቀቁ ብሎ አዝዞአልና ሺህ ብር በእጄ ላይ ብትመዝን እጄን በንጉሡ ልጅ ላይ ባልዘረጋሁም ነበር።
- 13
እኔ ቅሉ በነብሱ ላይ ብወነጅል ኖሮ ይህ ከንጉሥ ባልተሰወረም፥ አንተም በተነሳህብኝ ነበር አለው።
- 14
ኢዮአብም። እኔ ከአንተ ጋር እንዲህ እዘገይ ዘንድ አልችልም ብሎ ሦስት ጦሮች በእጁ ወሰደ፥ አቤሴሎምም ገና በዛፍ ላይ ተንጠልጥሎ ሕያው ሳለ በልቡ ላይ ተከላቸው።
- 15
አስሩም የኢዮአብ ጋሻ ጃግሬዎች ከበቡት፥ አቤሴሎምንም መትተው ገደሉት።
- 16
ኢዮአብም ሕዝቡን ከልክሎ ነበርና ቀንደ መለከት ነፋ፥ ሕዝቡም እስራኤልን ከማሳደድ ተመለሰ።
- 17
አቤሴሎምንም ወስደው በዱር ባለ በታላቅ ጕድጓድ ውስጥ ጣሉት፥ እጅግም ታላቅ የሆነ የድንጋይ ክምር ከመሩበት፤ እስራኤልም ሁሉ እያንዳንዱ ወደ ድንኳኑ ሸሸ።
- 18
አቤሴሎምም ሕያው ሳለ። ለስሜ መታሰቢያ የሚሆን ልጅ የለኝም ብሎ ሃውልት ወስዶ በንጉሥ ሸለቆ ውስጥ ለራሱ አቁሞ ነበር፤ ሃውልቱንም በስሙ ጠርቶት ነበር፤ እስከ ዛሬም ድረስ የአቤሴሎም መታሰቢያ ተብሎ ይጠራል።
- 19
የሳዶቅ ልጅ አኪማኣስ ግን። እግዚአብሔር ጠላቶቹን እንደተበቀለለት ሮጬ ለንጉሥ የምሥራች ልንገር አለ።
- 20
ኢዮአብም። በሌላ ቀን እንጂ ዛሬ ወሬ አትናገርም፤ የንጉሥ ልጅ ሞቶአልና ዛሬ ወሬ አትናገርም አለው።
- 21
ኢዮአብም ኵሲን። ሂድ ያየኸውንም ለንጉሡ ንገር አለው። ኵሲም ለኢዮአብ እጅ ነስቶ ሮጠ።
- 22
ዳግመኛም የሳዶቅ ልጅ አኪማአስ ኢዮአብን። የሆነ ሆኖ ኵሲን ተከትዬ፥ እባክህ፥ ልሩጥ አለው። ኢዮአብም። ልጄ ሆይ፥ መልካም ወሬ የምትወስድ አይደለህምና ትሮጥ ዘንድ ለምን ትወድዳለህ? አለ።
- 23
እርሱም። እኔ ብሮጥ ምን ይገድዳል? አለ። እርሱም። ሩጥ አለው። አኪማአስም በሜዳው መንደር በኩል ሮጠ፥ ኵሲንም ቀደመው።
- 24
ዳዊትም በሁለት በር መካከል ተቀምጦ ነበር፤ ዘበኛውም በቅጥሩ ላይ ወዳለው ወደ በሩ ሰገነት ወጣ፥ ዓይኑንም አቅንቶ ብቻውን የሚሮጥ ሰው አየ።
- 25
ዘበኛውም ለንጉሡ ሊነግረው ጮኸ። ንጉሡም። ብቻውን እንደሆነ በአፉ ወሬ ይኖራል አለ።
- 26
እርሱም ፈጥኖ ቀረበ። ዘበኛውም ሌላ ሰው ሲሮጥ አየ፤ ዘበኛውም ለደጅ ጠባቂው ጮኾ። እነሆ፥ ብቻውን የሚሮጥ ሌላ ሰው አየሁ አለ። ንጉሡም። እርሱ ደግሞ ወሬ ይዞ ይሆናል አለ።
- 27
ዘበኛውም። የፊተኛው ሩጫ እንደ ሳዶቅ ልጅ እንደ አኪማአስ ሩጫ ይመስላል አለ፤ ንጉሡም። እርሱ መልካም ሰው ነው፥ መልካምም ወሬ ያመጣል አለ።
- 28
አኪማአስም ጮኾ ንጉሡን። ሁሉ ደህና ሆኖአል አለው። በንጉሡም ፊት በምድር ላይ በግምባሩ ተደፍቶ። በንጉሡ በጌታዬ ላይ እጃቸውን ያነሱትን ሰዎች አሳልፎ የሰጠ አምላክህ እግዚአብሔር ይመስገን አለ።
- 29
ንጉሡም። ብላቴናው አቤሴሎም ደህና ነውን? አለ። አኪማአስም። ኢዮአብ እኔን ባሪያህንና የንጉሡን ባሪያ በላከ ጊዜ ትልቅ ሽብር አይቻለሁ፥ ምን እንደሆነ ግን አላወቅሁም ብሎ መለሰለት።
- 30
ንጉሡም። ፈቀቅ ብለህ ቁም አለ፤ እርሱም ፈቀቅ ብሎ ቆመ።
- 31
እነሆም፥ ኵሲ መጣ፤ ኵሲም። እግዚአብሔር በላይህ የተነሡትን ሁሉ ዛሬ እንደተበቀለልህ ለጌታዬ ለንጉሡ ወሬ አምጥቻለሁ አለ።
- 32
ንጉሡም ኵሲን። ብላቴናው አቤሴሎም ደህና ነውን? አለው። ኵሲም። የጌታዬ የንጉሡ ጠላቶች፥ በክፉም የተነሡብህ ሁሉ እንደዚያ ብላቴና ይሁኑ ብሎ መለሰለት።
- 33
ንጉሡም እጅግ አዘነ፥ በበሩም ላይ ወዳለችው ቤት ወጥቶ አለቀሰ፤ ሲሄድም። ልጄ አቤሴሎም ሆይ፥ ልጄ፥ ልጄ አቤሴሎም ሆይ፥ በአንተ ፋንታ ሞቼ ኖሮ ቢሆን፥ ልጄ አቤሴሎም፥ ልጄ ሆይ ይል ነበር። ች