2 Samuel 16
World English Bible (en) → Amharic Bible (am)
- 1
ዳዊትም ከተራራው ራስ ጥቂት ፈቀቅ ባለ ጊዜ የሜምፊቦስቴ ባሪያ ሲባ ሁለት መቶ እንጀራ፥ አንድ መቶም ዘለላ ዘቢብ፥ አንድ መቶም በለስ፥ አንድ አቁማዳም ወይን ጠጅ የተጫኑ ሁለት አህዮች እየነዳ ተገናኘው።
- 2
ንጉሡም ሲባን። ይህ ምንድር ነው? አለው። ሲባም። አህዮቹ የንጉሥ ቤተ ሰቦች ይቀመጡባቸው ዘንድ፥ እንጀራውና በለሱ ብላቴኖቹ ይበሉት ዘንድ፥ የወይን ጠጁም በበረሀ የሚደክሙት ይጠጡት ዘንድ ነው አለ።
- 3
ንጉሡም። የጌታህ ልጅ ወዴት ነው? አለ። ሲባም ንጉሡን። እነሆ። የእስራኤል ቤት ዛሬ የአባቴን መንግሥት ይመልስልኛል ብሎ በኢየሩሳሌም ተቀምጦአል አለው።
- 4
ንጉሡም ሲባን። እነሆ፥ ለሜምፊቦስቴ የነበረው ሁሉ ለአንተ ይሁን አለው። ሲባም። እጅ እነሣለሁ፤ ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፥ በፊትህ ሞገስ ላግኝ አለ።
- 5
ንጉሡ ዳዊትም ወደ ብራቂም መጣ፤ እነሆም፥ ሳሚ የሚባል የጌራ ልጅ ከሳኦል ቤተ ዘመድ የሆነ አንድ ሰው ከዚያ ወጣ፥ እየሄደም ይረግመው ነበር።
- 6
ወደ ዳዊትና ወደ ንጉሡ ወደ ዳዊት ባሪያዎችም ድንጋይ ይወረውር ነበር፤ በንጉሡም ቀኝና ግራ ሕዝቡ ሁሉና ኃያላኑ ሁሉ ነበሩ።
- 7
ሳሚም ሲረግም። ሂድ፥ አንተ የደም ሰው፥ ምናምንቴ፥ ሂድ።
- 8
በፋንታው ነግሠሃልና እግዚአብሔር የሳኦልን ቤት ደም ሁሉ መለሰብህ፤ እግዚአብሔርም መንግሥትን ለልጅህ ለአቤሴሎም እጅ አሳልፎ ሰጥቶታል፤ እነሆም፥ አንተ የደም ሰው ነህና በመከራ ተይዘሃል አለ።
- 9
የጽሩያም ልጅ አቢሳ ንጉሡን። ይህ የሞተ ውሻ ጌታዬን ንጉሡን ስለምን ይረግማል? ልሂድና ራሱን ልቍረጠው አለው።
- 10
ንጉሡም። እናንተ የጽሩም ልጆች፥ እኔ ከእናንተ ጋር ምን አለኝ? እግዚአብሔር። ዳዊትን ስደበው ብሎ አዝዞታልና ይርገመኝ፤ ለምንስ እንዲህ ታደርጋለህ? የሚለው ማን ነው? አለ።
- 11
ዳዊትም አቢሳንና ባሪያዎቹን ሁሉ። እነሆ ከወገቤ የወጣው ልጄ ነፍሴን ይሻል፤ ይልቁንስ ይህ የብንያም ልጅ እንዴት ነዋ? እግዚአብሔር አዝዞታልና ተዉት፥ ይርገመኝ።
- 12
ምናልባት በዚህ ቀን መከራዬን አይቶ ስለ እርግማኑ መልካም ይመልስልኛል አላቸው።
- 13
ዳዊትና ሰዎቹም በመንገድ ይሄዱ ነበር፤ ሳሚም በተራራው አጠገብ በእርሱ ትይዩ እየሄደ ይራገም፤ ድንጋይም ይወረውር፥ ትቢያም ይበትን ነበር።
- 14
ንጉሡና ከእርሱም ጋር የነበረው ሕዝብ ሁሉ ደክመው ነበር፥ በዚያም ዐረፉ።
- 15
አቤሴሎምና ሕዝቡ ሁሉ የእስራኤልም ሰዎች አኪጦፌልም ወደ ኢየሩሳሌም መጡ።
- 16
የዳዊትም ወዳጅ አርካዊው ኩሲ ወደ አቤሴሎም በመጣ ጊዜ ኩሲ። ሺህ ዓመት ያንግሥህ አለው።
- 17
አቤሴሎምም ኩሲን። ስለ ወዳጅህ ያደረግኸው ቸርነት ይህ ነውን? ከወዳጅህ ጋር ያልሄድህ ስለምንድር ነው? አለው።
- 18
ኩሲም አቤሴሎምን። እንዲህ አይደለም፤ ከእግዚአብሔር ከዚህም ሕዝብ ከእስራኤልም ሰዎች ሁሉ ለተመረጠው ለእርሱ እሆናለሁ ከእርሱም ጋር እቀመጣለሁ።
- 19
ዳግምም የማገለግል ለማን ነው? በንጉሥ ልጅ ፊት አይደለምን? በአባትህ ፊት እንዳገለገልሁ እንዲሁ በአንተ ፊት እሆናለሁ አለው።
- 20
አቤሴሎምም አኪጦፌልን። ምከሩ ምን እናድርግ? አለው።
- 21
አኪጦፌልም አቤሴሎምን። ቤት ሊጠብቁ ወደ ተዋቸው ወደ አባትህ ቁባቶች ግባ፤ እስራኤልም ሁሉ አባትህን እንዳሳፈርኸው ይሰማሉ፤ ከአንተም ጋር ያሉት ሁሉ እጃቸው ይበረታል አለው።
- 22
ለአቤሴሎምም በሰገነት ላይ ድንኳን ተከሉለት፤ አቤሴሎምም በእስራኤል ሁሉ ፊት ወደ አባቱ ቁባቶች ገባ።
- 23
በዚያም ወራት የመከራት የአኪጦፌል ምክር የእግዚአብሔርን ቃል እንደ መጠየቅ ነበረች፤ የአኪጦፌልም ምክር ሁሉ ከዳዊትና ከአቤሴሎም ጋር እንዲህ ነበረች።