1 Samuel 27
World English Bible (en) → Amharic Bible (am)
- 1
ዳዊትም በልቡ። አንድ ቀን በሳኦል እጅ እጠፋለሁ፤ ወደ ፍልስጥኤማውያንም ምድር ከመሸሽ በቀር የሚሻለኝ የለም፤ ሳኦልም በእስራኤል አውራጃ ሁሉ እኔን መሻት ይተዋል፥ እንዲሁም ከእጁ እድናለሁ አለ።
- 2
ዳዊትም ከእርሱም ጋር የነበሩት ስድስቱ መቶ ሰዎች ተነሥተው ወደ ጌት ንጉሥ ወደ አሜህ ልጅ ወደ አንኩስ አለፉ።
- 3
ዳዊትና ሰዎቹም እያንዳንዳቸው ከነ ቤተ ሰቡ ከአንኩስ ጋር በጌት ውስጥ ተቀመጡ፤ ከዳዊትም ጋር ኢይዝራኤላዊቱ አኪናሆምና የቀርሜሎሳዊው የናባል ሚስት አቢግያ ሁለቱ ሚስቶቹ ነበሩ።
- 4
ሳኦልም ዳዊት ወደ ጌት እንደ ኰበለለ ሰማ፤ ከዚያም በኋላ ደግሞ አልፈለገውም።
- 5
ዳዊትም አንኩስን። በዓይንህ ፊት ሞገስ አግኝቼ እንደ ሆነ በዚህ አገር በአንዲቱ ከተማ የምቀመጥበት ስፍራ ስጠኝ፤ ስለ ምን እኔ ባሪያህ ከአንተ ጋር በንጉሥ ከተማ እቀመጣለሁ? አለው።
- 6
በዚያም ቀን አንኩስ ጺቅላግን ሰጠው፤ ስለዚህም ጺቅላግ እስከ ዛሬ ድረስ ለይሁዳ ነገሥታት ሆነች።
- 7
ዳዊትም በፍልስጥኤማውያን አገር የተቀመጠበት የዘመን ቍጥር አንድ ዓመት ከአራት ወር ነበረ።
- 8
ዳዊትና ሰዎቹም ወጥተው በጌሹራውያንና በጌርዛውያን በአማሌቃውያንም ላይ ዘመቱ፤ እነዚህም እስከ ሱር እስከ ግብጽ ምድር ድረስ ባለው አገር ድሮውኑ ተቀምጠው ነበር።
- 9
ዳዊትም ምድሪቱን መታ፤ ወንድ ሆነ ሴትም ሆነ ማንንም በሕይወት አልተወም፤ በጎችንና ላሞችን አህያዎችንና ግመሎችን ልብስንም ማረከ፥ ተመልሶም ወደ አንኩስ መጣ።
- 10
አንኩስም። ዛሬ በማን ላይ ዘመታችሁ? አለ፤ ዳዊትም። በይሁዳ ደቡብ፥ በይረሕምኤላውያንም ደቡብ፥ በቄናውያንም ደቡብ ላይ ዘመትን አለ።
- 11
ዳዊት እንዲህ አደረገ በፍልስጥኤማውያንም አገር በሚቀመጥበት ዘመን ሁሉ ልማዱ ይህ ነበረ ብለው እንዳይናገሩብን ብሎ ዳዊት ወደ ጌት ያመጣቸው ዘንድ ወንድም ሆነ ሴትም ሆነ ማንንም በሕይወት አልተወም።
- 12
አንኩስም። በሕዝቡ በእስራኤል ዘንድ እጅግ የተጠላ ሆኖአል፤ ስለዚህም ለዘላለም ባሪያ ይሆነኛል ብሎ ዳዊትን አመነው።