1 Samuel 20
World English Bible (en) → Amharic Bible (am)
- 1
ዳዊትም ከአርማቴም አገር ከነዋትዘራማ ሸሸ፥ ወደ ዮናታንም መጥቶ። ምን አደረግሁ? እኔንስ ለመግደል የሚፈልግ በአባትህ ፊት ጠማምነቴና ኃጢአቴ ምንድር ነው? ብሎ ተናገረው።
- 2
ዮናታንም። ይህንስ ያርቀው፥ አትሞትም፤ እነሆ፥ አባቴ አስቀድሞ ለእኔ ሳይገልጥ ትልቅም ትንሽም ነገር ቢሆን አያደርግም፤ አባቴስ ይህን ነገር ለምን ይሰውረኛል? እንዲህ አይደለም አለው።
- 3
ዳዊትም። እኔ በፊትህ ሞገስ እንዳገኘሁ አባትህ በእውነት ያውቃል፤ እርሱም። ዮናታን እንዳይከፋው አይወቅ ይላል፤ ነገር ግን ሕያው እግዚአብሔርን! በሕያው ነፍስህም እምላለሁ! በእኔና በሞት መካከል አንድ እርምጃ ያህል ቀርቶአል ብሎ ማለ።
- 4
ዮናታንም ዳዊትን። ነፍስህ የወደደችውን ሁሉ አደርግልሃለሁ አለው።
- 5
ዳዊትም ዮናታንን አለው። እነሆ፥ ነገ መባቻ ነው፤ በንጉሥም አጠገብ ለምሳ አልቀመጥም፤ እስከ ሦስተኛው ቀን ማታ ድረስ በውጭ በሜዳ እንድሸሸግ አሰናብተኝ።
- 6
አባትህም ቢፈልገኝ። ለዘመዶቹ ሁሉ በዚያ በቤተ ልሔም የዓመት መሥዋዕት አላቸውና ዳዊት ወደ ከተማው ፈጥኖ ይሄድ ዘንድ አጽንቶ ለምኖኛል በለው።
- 7
እርሱም። መልካም ነው ቢል ለእኔ ለባሪያህ ደኅንነት ይሆናል፤ ቢቈጣ ግን ክፋት ከእርሱ ዘንድ በእኔ ላይ እንደ ተቈረጠች እወቅ።
- 8
እንግዲህ የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ከባሪያህ ጋር አድርገሃልና ለባሪያህ ቸርነት አድርግ፤ በደል ግን ቢገኝብኝ አንተ ግደለኝ፤ ለምን ወደ አባትህ ታደርሰኛለህ?
- 9
ዮናታንም። ይህ ከአንተ ይራቅ፤ ከአባቴ ዘንድ ክፋት በላይህ እንደ ተቈጠረች ያወቅሁ እንደ ሆነ አልነግርህምን? አለ።
- 10
ዳዊትም ዮናታንን። አባትህ ስለ እኔ ክፉ ነገር የነገረህ እንደ ሆን ማን ይነግረኛል? አለው።
- 11
ዮናታንም ዳዊትን። ና ወደ ሜዳ እንውጣ አለው። ሁለቱም ወደ ሜዳ ወጡ።
- 12
ዮናታንም ዳዊትን አለው። የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ምስክር ይሁን፤ ነገ ወይም ከነገ ወዲያ በዚህ ጊዜ አባቴን መርምሬ፥ እነሆ፥ በዳዊት ላይ መልካም ቢያስብ ልኬ እገልጥልሃለሁ፤
- 13
አባቴም በአንተ ላይ ክፋት ማድረግ ቢወድድ እኔም ባላስታውቅህ በደህና ትሄድ ዘንድ ባላሰናብትህ፥ እግዚአብሔር በዮናታን ይህን ያድርግ ይህንም ይጨምር፤ እግዚአብሔርም ከአባቴ ጋር እንደ ነበረ ከአንተ ጋር ይሁን።
- 14
እኔም እንዳልሞት በሕይወቴ ዘመን የእግዚአብሔርን ቸርነት አድርግልኝ፤
- 15
ደግሞም እግዚአብሔር የዳዊትን ጠላቶች ሁሉ እያንዳንዱ ከምድር ባጠፋቸው ጊዜ ለዘላለም ቸርነትህን ከቤቴ አታርቀው።
- 16
ዮናታንም። እግዚአብሔር ከዳዊት ጠላቶች እጅ ይፈልገው ብሎ ከዳዊት ቤት ጋር ቃል ኪዳን አደረገ።
- 17
ዮናታንም ዳዊትን እንደ ነፍሱ ይወድድ ነበርና እንደ ገና ማለለት።
- 18
ዮናታንም አለው። ነገ መባቻ ነው፥ መቀመጫህም ባዶ ሆኖ ይገኛልና ትታሰባለህ።
- 19
ሦስት ቀንም ያህል ቆይ፤ ከዚህም በኋላ ፈጥነህ ውረድ፥ ነገሩም በተደረገበት ቀን ወደ ተሸሸግህበት ስፍራ ሂድ፥ በኤዜል ድንጋይም አጠገብ ቆይ።
- 20
እኔም በዓላማ ላይ እወረውራለሁ ብዬ ሦስት ፍላጻዎችን ወደ አጠገቡ እወረውራለሁ።
- 21
እነሆም። ሂድ ፍላጻዎችን ፈልግ ብዬ ብላቴናውን እልከዋለሁ፤ ብላቴናውንም። እነሆ፥ ፍላጻው ከአንተ ወደዚህ ነው፤ ይዘኸው ወደ እኔ ና ያልሁት እንደ ሆነ፥ ሕያው እግዚአብሔርን! ለአንተ ደኅንነት ነውና ምንም የለብህም።
- 22
ብላቴናውን ግን። እነሆ፥ ፍላጻው ከአንተ ወዲያ ነው ያልሁት እንደ ሆነ፥ እግዚአብሔር አሰናብቶሃልና መንገድህን ሂድ።
- 23
አንተና እኔም ስለ ተነጋገርነው፥ እነሆ፥ እግዚአብሔር ለዘላለም በመካከላችን ምስክር ነው።
- 24
ዳዊትም በሜዳው ተሸሸገ፤ መባቻም በሆነ ጊዜ ንጉሡ ግብር ለመብላት ተቀመጠ።
- 25
ንጉሡም እንደ ቀድሞው በግንቡ አጠገብ በዙፋኑ ላይ ተቀመጠ፤ ዮናታንም ቆሞ ነበር፥ አበኔርም በሳኦል አጠገብ ተቀመጠ፤ የዳዊትም ስፍራ ባዶውን ነበረ።
- 26
ሳኦልም። አንድ ነገር ሆኖአል፥ ንጹሕም አይደለም፤ በእውነት ንጹሕ አይደለም ብሎ አስቦአልና በዚያን ቀን ምንም አልተናገረም።
- 27
ከመባቻም በኋላ በማግሥቱ በሁለተኛው ቀን የዳዊት ስፍራ ባዶውን ነበረ፤ ሳኦልም ልጁን ዮናታንን። የእሴይ ልጅ ትናንትና ወይም ዛሬ ግብር ሊበላ ያልመጣ ስለ ምን ነው? አለው።
- 28
ዮናታንም ለሳኦል። ዳዊት ወደ ቤተ ልሔም ይሄድ ዘንድ አጽንቶ ለመነኝ፤
- 29
እርሱም። ዘመዶቼ በከተማ ውስጥ መሥዋዕት አላቸውና፥ ወንድሜም ጠርቶኛልና እባክህ፥ አሰናብተኝ፤ አሁንም በዓይኖችህ ሞገስ አግኝቼ እንደ ሆነ ልሂድና ወንድሞቼን ልይ አለ፤ ስለዚህ ወደ ንጉሥ ሰደቃ አልመጣም ብሎ መለሰለት።
- 30
የሳኦልም ቍጣ በዮናታን ላይ ነደደና። አንተ የጠማማ ሴት ልጅ፥ የእሴይን ልጅ ለአንተ ማፈርያ ለእናትህም ኀፍረተ ሥጋ ማፈርያ እንደ መረጥህ እኔ አላውቅምን?
- 31
የእሴይም ልጅ በምድር ላይ በሕይወት በሚኖርበት ዘመን ሁሉ አንተና መንግሥትህ አትጸኑም፤ አሁንም የሞት ልጅ ነውና ልከህ አስመጣልኝ አለው።
- 32
ዮናታንም ለአባቱ ለሳኦል። ስለ ምን ይሞታል? ያደረገውስ ምንድር ነው? ብሎ መለሰለት።
- 33
ሳኦልም ሊወጋው ጦሩን ወረወረበት፤ ዮናታንም አባቱ ዳዊትን ፈጽሞ ሊገድለው እንደ ፈቀደ አወቀ።
- 34
አባቱ ዳዊትን ስላሳፈረው ዮናታን ስለ ዳዊት አዝኖአልና እጅግ ተቈጥቶ ከሰደቃው ተነሣ፥ በመባቻውም በሁለተኛ ቀን ግብር አልበላም።
- 35
እንዲህም ሆነ፤ በነጋው ዮናታን ከዳዊት ጋር ወደ ተቃጠረበት ቦታ ወደ ሜዳ ወጣ፥ ከእርሱም ጋር ታናሽ ብላቴና ነበረ።
- 36
ብላቴናውንም። ሮጠህ የምወረውራቸውን ፍላጻዎች ፈልግልኝ አለው። ብላቴናውም በሮጠ ጊዜ ፍላጻውን ወደ ማዶ ወረወረው።
- 37
ብላቴናውም ዮናታን ፍላጻውን ወደ ወረወረበት ስፍራ በመጣ ጊዜ ዮናታን። ፍላጻው ከአንተ ወዲያ ነው ብሎ ወደ ብላቴናው ጮኸ።
- 38
ዮናታንም ደግሞ። ቶሎ ፍጠን፥ አትቆይ ብሎ ወደ ብላቴናው ጮኸ፤ የዮናታንም ብላቴና ፍላጻዎቹን ሰብስቦ ወደ ጌታው መጣ።
- 39
ዮናታንና ዳዊት ብቻ ነገሩን ያውቁ ነበር እንጂ ብላቴናው ምንም አያውቅም ነበር።
- 40
ዮናታንም መሣርያውን ለብላቴናው ሰጥቶ። ወደ ከተማ ውሰድ አለው።
- 41
ብላቴናውም በሄደ ጊዜ ዳዊት ከስፍራው በደቡብ አጠገብ ተነሣ፥ በምድርም ላይ በግምባሩ ተደፋ፥ ሦስት ጊዜም ለሰላምታ ሰገደ፤ እየተላቀሱም እርስ በእርሳቸው ተሳሳሙ፥ ይልቁንም ዳዊት እጅግ አለቀሰ።
- 42
ዮናታንም ዳዊትን። በደኅና ሂድ፤ እነሆ፥ እኛ ሁለታችን በእኔና በአንተ፥ በዘሬና በዘርህ መካከል ለዘላለም እግዚአብሔር ይሁን ብለን በእግዚአብሔር ስም ተማምለናል አለው። ዳዊትም ተነሥቶ ሄደ፤ ዮናታንም ወደ ከተማ ገባ።