1 Chronicles 23
World English Bible (en) → Amharic Bible (am)
- 1
ዳዊትም በሸመገለ ጊዜ፥ ዕድሜንም በጠገበ ጊዜ ልጁን ሰሎሞንን በእስራኤል ላይ አነገሠው።
- 2
የእስራኤልንም አለቆች ሁሉ፥ ካህናቱንም፥ ሌዋውያኑንም ሰበሰበ።
- 3
ሌዋውያንም ከሠላሳ ዓመት ዕድሜ ጀምሮ ወደ ላይ ተቈጠሩ፤ ቍጥራቸው በእያንዳንዱ ነፍስ ወከፍ ሠላሳ ስምንት ሺህ ነበረ።
- 4
ከእነዚህም ውስጥ የእግዚአብሔርን ቤት ሥራ የሚያሠሩት ሀያ አራት ሺህ ነበሩ፤ ስድስቱ ሺህም አለቆችና ፈራጆች ነበሩ።
- 5
አራቱ ሺህም በረኞች ነበሩ፤ አራቱ ሺህም ለምስጋና በተሠሩት በዜማ ዕቃዎች እግዚአብሔርን ያመሰግኑ ነበር።
- 6
ዳዊትም እንደ ሌዊ ልጆች እንደ ጌድሶንና እንደ ቀዓት እነደ ሜራሪም በየሰሞናቸው ከፈላቸው።
- 7
ከጌድሶናውያን ለአዳንና ሰሜኢ ነበሩ።
- 8
የለአዳን ልጆች አለቃው ይሒኤል፥ ዜቶም፥ ኢዮኤል ሦስት ነበሩ።
- 9
የሰሜኢ ልጆች ሰሎሚት፥ ሐዝኤል፥ ሐራን ሦስት ነበሩ። እነዚህ የለአዳን አባቶች ቤቶች አለቆች ነበሩ።
- 10
የሰሜኢ ልጆች ኢኢት፥ ዚዛ፥ የዑስ፥ በሪዓ ነበሩ። እነዚህ አራቱ የሰሜኢ ልጆች ነበሩ።
- 11
አለቃው ኢኢት ነበረ፤ ሁለተኛው ዚዛ ነበረ፤ የዑስና በሪዓ ግን ብዙ ልጆች አልነበሩአቸውም፤ ስለዚህ እንደ አንድ አባት ቤት ሆነው ተቈጠሩ።
- 12
የቀአት ልጆች እንበረም፥ ይስዓር፥ ኬብሮን፥ ዑዝኤል አራት ነበሩ።
- 13
የእንበረም ልጆች አሮንና ሙሴ ነበሩ፤ አሮንም ከሁሉ በላይ የተቀደሰ ይሆን ዘንድ ተለየ፥ እርሱና ልጆቹ፥ ለዘላለም በእግዚአብሔር ፊት ያጥንና ያገለግል ዘንድ፥ በስሙም ለዘላለም ይባርክ ዘንድ።
- 14
የእግዚአብሔርም ሰው የሙሴ ልጆች በሌዊ ነገድ ተቈጠሩ።
- 15
የሙሴ ልጆች ጌርሳምና አልዓዛር ነበሩ።
- 16
የጌርሳም ልጆች አለቃ ሱባኤል ነበረ።
- 17
የአልዓዛርም ልጆች አለቃ ረዓብያ ነበረ፤ አልዓዛርም ሌሎች ልጆች አልነበሩትም፤ የረዓብያ ልጆች እጅግ ብዙ ነበሩ።
- 18
የይስዓር ልጆች አለቃው ሰሎሚት ነበረ።
- 19
የኬብሮን ልጆች አለቃው ይሪያ፥ ሁለተኛው አማርያ፥ ሦስተኛው የሕዚኤል፥ አራተኛው ይቅምዓም ነበሩ።
- 20
የዑዝኤል ልጆች አለቃው ሚካ፥ ሁለተኛው ይሺያ ነበሩ።
- 21
የሜራሪ ልጆች ሞሖሊና ሙሲ ነበሩ። የሞሖሊ ልጆች አልዓዛርና ቂስ ነበሩ።
- 22
አልዓዛርም ሴቶች ልጆች ብቻ እንጂ ወንዶች ልጆች ሳይወልድ ሞተ፤ ወንድሞቻቸውም የቂስ ልጆች አገቡአቸው።
- 23
የሙሲ ልጆች ሞሖሊ፥ ዔደር፥ ኢያሪሙት ሦስት ነበሩ።
- 24
የእግዚአብሔርን ቤት አገልግሎት በሠሩ ከሀያ ዓመት ዕድሜ ጀምሮ ወደ ላይ በነበሩ በእያንዳንዳቸው በስማቸው በተቆጠሩት ላይ የአባቶች ቤት አለቆች የሆኑት በየአባቶቻቸው ቤት የሌዊ ልጆች እነዚህ ነበሩ።
- 25
ዳዊትም። የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ለሕዝቡ ዕረፍት ሰጥቶአል፥ በኢየሩሳሌምም ለዘላለም የቀመጣል።
- 26
ሌዋውያንም ከእንግዲህ ወዲህ ማደሪያውንና የማገልገያውን ዕቃ ሁሉ አይሸከሙም አለ።
- 27
በመጨረሻውም በዳዊት ትእዛዝ ከሀያ ዓመት ዕድሜ ጀምሮ ከዚያም በላይ ያሉት የሌዊ ልጆች ተቈጠሩ።
- 28
ሥራቸውም የእግዚአብሔርን ቤት በየአደባባዩና በየጓዳው ውስጥ ለማገልገል፥ ቅዱሱንም ዕቃ ሁሉ ለማንጻት፥ የእግዚአብሔርንም ቤት አገልግሎት ለመሥራት ከአሮን ልጆች እጅ በታች ነበረ።
- 29
ደግሞም ገጸ ኅብስት፥ ስስ ቂጣም ቢሆን፥ በምጣድም ቢጋገር፥ ቢለወስም፥ ለእህል ቍርባን በሆነው በመልካሙ ዱቄት በመስፈሪያና በልክ ሁሉ ያገለግሉ ነበር።
- 30
ሥራቸውም በየጥዋቱና በየማታው ቆመው እግዚአብሔርን ለማመስገንና ለማክበር፥
- 31
በየሰንበታቱም በየመባቻዎቹም በየበዓላቱም እንደ ሥርዓቱ ቍጥር በእግዚአብሔር ፊት ዘወትር ለእግዚአብሔር የሚቃጠለውን መሥዋዕት ሁሉ ለማቅረብ፥
- 32
ለእግዚአብሔርም ቤት አገልግሎት የመገናኛውን ድንኳን ሥርዓት የመቅደሱንም ሥርዓት የወንድሞቻቸውንም የአሮንን ልጆች ሥርዓት ለመጠበቅ ነበረ።