1 Chronicles 15
World English Bible (en) → Amharic Bible (am)
- 1
ዳዊትም በከተማው ላይ ለራሱ ቤቶችን ሠራ፤ ለእግዚአብሔርም ታቦት ስፍራ አዘጋጀ፥ ድንኳንም ተከለለት።
- 2
በዚያን ጊዜም ዳዊት። የእግዚአብሔርን ታቦት ይሸከሙ ዘንድ፥ ለዘላለሙም ያገለግሉት ዘንድ እግዚአብሔር ከመረጣቸው ከሌዋውያን በቀር ማንም የእግዚአብሔርን ታቦት ይሸከም ዘንድ አይገባውም አለ።
- 3
ዳዊትም ወዳዘጋጀለት ስፍራ የእግዚአብሔርን ታቦት ያመጣ ዘንድ እስራኤልን ሁሉ ወደ ኢየሩሳሌም ሰበሰበ።
- 4
ዳዊትም የአሮንን ልጆችና ሌዋውያንን ሰበሰበ።
- 5
ከቀዓት ልጆች፤ አለቃው ኡርኤል፥ ወንድሞቹም መቶ ሀያ፤
- 6
ከሜራሪ ልጆች፤ አለቃው ዓሣያ፥ ወንድሞቹም ሁለት መቶ ሀያ፤
- 7
ከጌድሶን ልጆች፤ አለቃው ኢዮኤል፥ ወንድሞቹም መቶ ሠላሳ፤
- 8
ከኤሊጻፋን ልጆች፤ አለቃው ሸማያ፥ ወንድሞቹም ሁለት መቶ፤
- 9
ከኬብሮን ልጆች፤ አለቃው ኤሊኤል፥ ወንድሞቹም ሰማንያ፤
- 10
ከዑዝኤል ልጆች፤ አለቃው አሚናዳብ፥ ወንድሞቹም መቶ አሥራ ሁለት።
- 11
ዳዊትም ካህናቱን ሳዶቅንና አቢያታርን፥ ሌዋውያንንም ኡርኤልን፥ ዓሣያን፥ ኢዮኤልን፥ ሸማያን፥ ኤሊኤልን፥ አሚናዳብንም ጠርቶ።
- 12
እናንተ የሌዋውያን አባቶች ቤቶች አለቆች ናችሁ፤ ወዳዘጋጀሁለት ስፍራ የእስራኤልን አምላክ የእግዚአብሔርን ታቦት ታመጡ ዘንድ እናንተና ወንድሞቻችሁ ተቀደሱ።
- 13
ቀድሞም አልተሸከማችሁምና፥ እንደ ሥርዓቱም አልፈለግነውምና አምላካችን እግዚአብሔር በመካከላችን ስብራት አደረገ አላቸው።
- 14
የእስራኤልንም አምላክ የእግዚአብሔርን ታቦት ያመጡ ዘንድ ካህናቱና ሌዋውያኑ ተቀደሱ።
- 15
ሙሴም እንዳዘዘው እንደ እግዚአብሔር ቃል የሌዋውያን ልጆች የእግዚአብሔርን ታቦት በትከሻቸው ላይ በመሎጊያዎቹ ተሸከሙ።
- 16
ዳዊትም በዜማ ዕቃ በመሰንቆና በበገና በጸናጽልም እንዲያዜሙ፥ ድምፃቸውንም በደስታ ከፍ እንዲያደርጉ መዘምራኑን ወንድሞቻቸውን ይሾሙ ዘንድ ለሌዋውያን ኣለቆች ተናገረ።
- 17
ሌዋውያኑም የኢዮኤልን ልጅ ኤማንን፥ ከወንድሞቹም የበራክያን ልጅ አሳፍን፥ ከወንድሞቻቸውም ከሜራሪ ልጆች የቂሳን ልጅ ኤታንን፥
- 18
ከእነርሱም ጋር በሁለተኛው ተራ የሆኑትን ወንድሞቻቸውን ዘካርያስን፥ ቤንን፥ ያዝኤልን፥ ሰሚራሞትን፥ ይሒኤልን፥ ዑኒን፥ ኤልያብን፥ በናያስን፥ መዕሤያን፥ መቲትያን፥ ኤሊፍሌሁን፥ ሚቅንያን፥ በረኞችንም ዖቤድኤዶምንና ይዒኤልን አቆሙ።
- 19
መዘምራንም ኤማንና አሳፍ ኤታንም በናስ ጸናጽል ከፍ አድርገው ያሰሙ ነበር።
- 20
ዘካርያስ፥ ዓዝዔል፥ ሰሚራሞት፥ ይሒኤል፥ ዑኒ፥ ኤልያብ፥ መዕሤያ፥ በናያስ በመሰንቆ ምሥጢር ነገር ያዜሙ ነበር።
- 21
መቲትያ፥ ኤልፍሌሁ፥ ሚቅኒያ፥ ዖቤድኤዶም፥ ይዒኤል፥ ዓዛዝያ ስምንት አውታር ባለው በገና ይዘምሩ ነበር።
- 22
የሌዋውያኑም አለቃ ክናንያ በዜማ ላይ ተሹሞ ነበር። ብልሃተኛ ነበረና ዜማ ያስተምራቸው ነበር።
- 23
በራክያና ሕልቃናም ለታቦቱ በረኞች ነበሩ።
- 24
ካህናቱም ሰበንያ፥ ኢዮሳፍጥ፥ ናትናኤል፥ ዓማሣይ፥ ዘካርያስ፥ በናያስ፥ አልዓዛር በእግዚአብሔር ታቦይ ፊት መለከት ይነፉ ነበር። ዖቤድኤዶምና ይሒያም ለታቦቱ በረኞች ነበሩ።
- 25
ዳዊትም፥ የእስራኤልም ሽማግሌዎች፥ የሻለቆችም የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳኑን ታቦት ከአቢዳራ ቤት በደስታ ያመጡ ዘንድ ሄዱ።
- 26
የእግዚአብሔርንም ቃል ኪዳን ታቦት የተሸከሙትን ሌዋውያንን እግዚአብሔር በረዳቸው ጊዜ ሰባት በሬዎችና ሰባት አውራ በጎች ሰዉ።
- 27
ዳዊትም፥ ታቦቱንም የተሸከሙ ሌዋውያን ሁሉ፥ መዘምራኑም፥ የመዘምራኑም አለቃ ከናንያ የጥሩ በፍታ ቀሚስ ለብሰው ነበር፤ ዳዊትም የበፍታ ኤፉድ ነበረው።
- 28
እንዲሁ እስራኤል ሁሉ ሆ እያሉ ቀንደ መለከትና እምቢልታ እየነፉ፥ ጸናጽልና መሰንቆም በገናም እየመቱ፥ የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳን ታቦት አመጡ።
- 29
የእግዚአብሔርም ቃል ኪዳን ታቦት ወደ ዳዊት ከተማ በደረሰ ጊዜ የሳኦል ልጅ ሜልኮል በመስኮት ሆና ተመለከተች፤ ንጉሡም ዳዊት ሲዘፍንና ሲጫወት አይታ በልቧ ናቀችው።