1 Chronicles 13
World English Bible (en) → Amharic Bible (am)
- 1
ዳዊትም ከሻለቆችና ከመቶ አለቆች ከአለቆቹም ሁሉ ጋር ተማከረ።
- 2
ዳዊትም የእስራኤልን ጉባኤ ሁሉ። መልካም መስሎ የታያችሁ እንደሆነ፥ ከአምላካችን ከእግዚአብሔርም ወጥቶ እንደ ሆነ፥ በእስራኤል አገር ሁሉ ለቀሩት ወንድሞቻችን በከተሞቻቸውና በመሰምሪያዎቻቸውም ለሚቀመጡ ካህናትና ሌዋውያን ወደ እኛ ይሰበሰቡ ዘንድ እንላክ፤
- 3
በሳኦልም ዘመን አልፈለግነውምና የአምላካችንን ታቦት ወደ እኛ እንመልስ አላቸው።
- 4
ነገሩም በሕዝቡ ሁሉ ዓይን ዘንድ ቅን ነበረና ጉባኤው ሁሉ። እንዲሁ እናደርጋለን አሉ።
- 5
የእግዚአብሔርንም ታቦት ከቂርያትይዓሪም ያመጡ ዘንድ ዳዊት እስራኤልን ሁሉ ከግብጽ ወንዝ ከሺሖር ጀምሮ እስከ ሐማት መግቢያ ድረስ ሰበሰበ።
- 6
ዳዊትም እስራኤልም ሁሉ በኪሩቤል ላይ የተቀመጠውን ስሙም በእርሱ የተጠራውን የአምላክን የእግዚአብሔርን ታቦት ከዚያ ያወጡ ዘንድ በይሁዳ ወዳለችው ቂርያትይዓሪም ወደ ተባለች ወደ በኣላ ሄዱ።
- 7
የእግዚአብሔርንም ታቦት በአዲስ ሰረገላ ላይ ጫኑት፥ ከአሚናዳብም ቤት አመጡት፤ ዖዛና አሒዮም ሠረገላውን ይነዱ ነበር።
- 8
ዳዊትና እስራኤል ሁሉ በቅኔና በበገና በመሰንቆና በከበሮ በጸናጽልና በመለከት በእግዚአብሔር ፊት በሙሉ ኃይላቸው ይጫወቱ ነበር።
- 9
ወደ ኪዶንም አውድማ በደረሱ ጊዜ በሬዎቹ ይፋንኑ ነበርና ታቦቱን ሊይዝ ዖዛ እጁን ዘረጋ።
- 10
የእግዚአብሔርም ቍጣ በዖዛ ላይ ነደደ፥ እጁንም ወደ ታቦቱ ስለ ዘረጋ ቀሠፈው፤ በዚያም በእግዚአብሔር ፊት ሞተ።
- 11
እግዚአብሔርም ዖዛን ስለ ቀሠፈው ዳዊት አዘነ፤ እስከ ዛሬም ድረስ የዚያን ስፍራ ስም የዖዛ ስብራት ብሎ ጠራው።
- 12
በዚያም ቀን ዳዊት። የእግዚአብሔርን ታቦት ወደ እኔ እንዴት አመጣለሁ ብሎ እግዚአብሔርን ፈራ።
- 13
ዳዊትም ታቦቱን ወደ ጌት ሰው ወደ አቢዳራ ቤት አሳለፈው እንጂ ወደ እርሱ ወደ ዳዊት ከተማ አላመጣውም።
- 14
የእግዚአብሔርም ታቦት በአቢዳራ ቤተሰብ ዘንድ በቤቱ ውስጥ ሦስት ወር ተቀመጠ፤ እግዚአብሔርም የአቢዳራን ቤትና ያለውን ሁሉ ባረከ።